ኤስ አይ ኤል ዓለምአቀፋዊ፣ ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ አነስተኛ የተናጋሪ ቁጥር ያላቸውን ቋንቋዎች ለማልማት የቋንቋ ባለቤት ህብረተሰብ በቋንቋ ተጠቃሚ እንዲሆንና ዘላቂ የቋንቋ ክህሎትና አቅም እንዲገነባ ብሎም ህብረተሰቡ ባህሉንና ዕሴቱን እንዲንከባከብ ለማስቻል የተቋቋመ ድርጅት ነው። ኤስ አይ ኤል ማንኛውም ሃይማኖት፣ እምነት፣ ፖለቲካዊ፣ ርዕዮተ ዓለማዊ፣ የጾታና የብሔር ብሔረሰብ ማንነት ሳያግደው ሁሉንም ህብረተሰብ በእኩልነት የቋንቋና የባህል ልማቱን ለማዳበር በሚያደርገው ጥረት ሙያዊ እገዛ በመስጠት የአቅም ግንባታ ስልጠና የሚሰጥ ተቋም ነው።
- የቋንቋ ልማት
- ስነ–ልሳን
- መሠረታዊ የማንበብና መፃፍ ትምህርትና መደበኛ የልሳነ–ብዙ (ብዝሀ–ቋንቋ) ትምህርት
- የቋንቋን ልማት ቴክኖሎጂ ማገዝ
- አቅም ግንባታ
- በአጋርነትና በትብብር ማገልገል
የቋንቋ ልማት፦ የቋንቋው ተናጋሪ ህብረተሰብ ቋንቋው እንዲያድግና በየጊዜው እያደገ የሚሄደውን ፍላጎታቸውን ሊያሟላ እንዲችል ለማድረግ በቋንቋ ዕድገት ላይ ያለማቋረጥ የሚተገበር እንቅስቃሴ ነው።
ስነ–ልሳን፦ በመደበኛ የቋንቋ ትምህርት ለመሰረታዊ የማንበብና መጻፍ ትምህርት እና ለትርጉም ሥራ መሠረት የሆነ የቋንቋ ልማት ቀመር ተግባር ነው። በመስኩ የተሰማሩ የስነ-ልሳን ሠራተኞቻችን የቋንቋው ተናጋሪ ህብረተሰብ ስለ ቋንቋቸውና ስለባህሎቻቸው መረጃ በመሰብሰብ ጥናት እንዲያደርጉ የአቅም ግንባታ ስልጠና ይሰጣሉ። የቋንቋ ምርምር እና ጥናት በማድረግ ስነ ልሳናዊ ግምገማ እንዲካሄድና ተናጋሪዎች የቋንቋዎቻቸው ስርዓተ-ጽህፈት፣ ሰዋሰው እና መዝገበ ቃላት እንዲያዘጋጁና እንዲያውቁ እርዳታ ያደርጋሉ። በዚህም መሠረት የቋንቋዎቹን የጥናት ውጤት በማሳተም ሕብረተሰቡ እንዲጠቀምበት ጥረት እናደርጋለን። ከ2003 ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ በ24 የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የስነ-ልሳን ጥናትና ምርምር ከመሳተፋችን ባሻገር የ5 ቋንቋዎች መዝገበ ቃላት እንዲዘጋጁ ለሕብረተሰቡ የአቅም ግንባታ ስልጠናና ዕገዛ አድርገናል።
መሠረታዊ የማንበብና መፃፍ ትምህርትና መደበኛ የልሳነ–ብዙ (ብዝሀ–ቋንቋ) ትምህርት በዚህ መርሃ ግብር ውስጥ ድርጅታችን በመደበኛ ትምህርት ውስጥ ያሉ ህፃናት እና መደበኛ ባልሆነ ትምህርት መርሃግብር የሚማሩ ጎልማሶች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ አስፈላጊ ሙያዊ ድጋፍ ክትትልና ስልጠና ይሰጣል። በአፍ መፍቻ ቋንቋ ስነጽሁፎችን ለንባብ ማብቃትና ሕብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ የቋንቋ ልማቱን የሚያፋጥንና ቋንቋው ለበለጠ ግንኙነትና ተግባቦት መጠቀም ስለሚያስችል በዚህ ረገድ ሕብረተሰቡን በማገዝ ብቃት ያለው ሥራ እንሰራለን።
በልሳነ ብዙ (ብዝሀ ቋንቋ) ትምህርት አማካኝነት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሌሎች ትምህርቶችንና የትምህርት ቋንቋዎችን በብቃት እንዲማሩ ከሚመለከተው የመንግስት ድርጅቶች እና ትምህርት ቤቶች ጋር በትብብር እንሠራለን። በዚህ ስራችን ዋነኛው ተግባር የቋንቋው ተናጋሪ ህብረተሰብ ሕፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በመማር ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ የአካባቢውን የትምህርት ሴክተር መርዳት ነው። ከዚህም አንፃር ኤስ አይ ኤል ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ ቋንቋዎቸ በአፍ መፍቻ ትምህርት እንዲጀመርና ሕፃናት በሚያውቁት ቋንቋ እንዲማሩ በትምህርት ሚኒስቴር የየአካባቢው ተጠሪ መስሪያ ቤቶችን በማገዝና ስልጠና በመስጠት ከ1-4ኛ ክፍል የትምህርት መሳሪያዎች ዝግጅትና ስልጠና ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
የቋንቋን ልማት ቴክኖሎጂ ማገዝ
ከቋንቋ ዕድገትና ልማት ሥራ ውስጥ ሊካተት የሚገባውና እኛም በስፋት የምንሳተፍበት መስክ የቋንቋ ልማትን በቴክኖሎጂ የማገዝ ስራ ሲሆን ይህም የኮምፒውተርን ቴክኖሎጂ በስራ ውስጥ በመጠቀም ልዩ ልዩ ሶፍትዌሮችን ለስነጽሁፍ፣ ለህትመት ሥራ ማዋልን ያካትታል። ኢትዮጵያዊ ለሆኑና ለተሰማራንባቸው የቋንቋ ልማት ስራዎች ኪ-ቦርድ እናዘጋጃለን። በተጨማሪም የሶፍትዌር ልዩ ልዩ ስልጠናዎችን እንሰጣለን። (ፍሌክስ፣ የመስክ ስራ፣ ፕሪመር ፕሮ እና ፓራ ቴክስት) ፕሮግራሞች አጠቃቀምን እናስተዋውቃለን።
አቅም ግንባታ
በኤስ አይ ኤል ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያገለግሉ ባለሙያዎች ሁሉ ለቋንቋ ተጠቃሚ ህብረተሰብ የቋንቋ ስልጠና አውደጥናቶችና ስልጠናዎች በሚካሄዱበት ጊዜ ሙያዊና ቴክኒካዊ ድጋፍና ስልጠና በመስጠት ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። ከነዚህም ውስጥ ጥቂቶቹ፣ መዝገበ ቃላት አዘገጃጀት፣ የስነ-ልሳን አጠቃቀም፣ የትርጉም መርህ፣ የንባብና የጽሁፍ መጽሀፍቶች አዘገጃጀት የታሪክ አፃፃፍና መሠረታዊ የጽሁፍ መርሆዎች እና የአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት መማሪያ መጽሀፍት አዘገጃጀትን ያካተታሉ።
በአጋርነትና በትብብር ማገልገል
በግልጽ እንደሚታወቀው ሁሉ የቋንቋ ልማት ስራ በጋራና በህብረት የሚሰራ ስራ ነው። ኤስ አይ ኤል ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ልሳነ ብዙ ትምህርት ህብረት (MLE NETWORK) አባልና መስራች ድርጅት ነው። ከዚህ አንፃር በሌላም በበርካታ ሁኔታዎች ከመንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በትብብርና በመተጋገዝ እንሰራለን። ስለዚህም ከትምህርት ሚኒስቴር ከባህል ሚኒስቴርና ከልዩ ልዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ስምምነት ተፈራርመን በተባባሪነት በቋንቋ ልማት ስራዎች ላይ በጋራ እንሰራለን። ኤስ አይ ኤል በዓለም አቀፍ ደረጃ መንግስታዊ ካልሆኑ የUNESCO ተባባሪ ድርጅቶች አንዱ ነው።